ባህሪዬን መቀየር አለብኝ ብሎ ለማመን ብዙ ጥንካሬ ይጠይቃል።
ይህ ገጽ እርስዎ መሆን የሚችሉትን ምርጥ ወንድ፣ የኑሮ አጋር፣ አባት ወይም የቤተሰብ አባል ለመሆን በያዙት ጉዞ እንዴት ልንረዳዎት እንደምንችል ያብራራል።
እራስዎን ይጠይቁ፦
- አንድ የቤተሰብ አባልን ድምጼን ከፍ አድርጌ ተናግሬ ወይም ጮኼባቸው አውቃለሁ?
- የቤተሰብ አባልን መትቼ፣ በጥፊ መትቼ፣ በእርግጫ መትቼ፣ ገፍቼ ወይም ገፍትሬ ጥዬ ወይም ደግሞ እነዚህን ነገሮች አደርጋለሁ ብዬ አስፈራርቼ አውቃለሁ?
- የቤተሰብ አባልን በመጥፎ ወይም አክብሮት የጎድለው ስም ጠርቼ አውቃለሁ? ሁልጊዜም እየወቀስኳቸው ነው?
- የኑሮ አጋሬ ለራሳቸው ጥቅም ገንዘብ እንዳያወጡ ከልክዬ አውቃለሁ?
- የቤተሰብ አባልን እንዲፈሩ አድርጌ አውቃለሁ?
- እንደ ብርጭቆ፣ ወንበር ወይም የቲቪ ሪሞት ያሉ ነገሮችን የቤተሰብ አባል ፊት ወይም የቤተሰብ አባል ላይ ወርውዬ አውቃለሁ?
- የኑሮ አጋሬ ማድረግ የማይፈልጉትን ወሲባዊ ድርጊት እንዲያደርጉ ጫና አሳድሬ አውቃለሁ?
- የኑሮ አጋሬ የሚፈልጉትን ነገር እንዳያደርጉ ለማስቆም ሞክሬ አውቃለሁ? (ለምሳሌ ከጓደኞች ጋር መውጣት፣ ሥራ መያዝ፣ ትምህርት መማር)
- LGBTIQA+ የሆኑት የኑሮ አጋሬን የሥርዓተ-ፆታ ማንነት እንደማጋልጥ አስፈራቼ አውቃለሁ?
ከእነዚህ ጥያቄዎች ውስጥ አንድ ወይም ከዚያ በላይ ለሚሆኑት ምላሽዎ አዎ ከሆነ፣ ከታች የተቀመጡት አገልግሎቶቻችን ሊያግዙ ይችላሉ።
የወንዶች የሪፈራል አገልግሎት (Men’s Referral Service) – 1300 766 491
በቀን ለ24 ሰዓት፣ በዓመት ለ365 ቀናት የሚገኝ
የወንዶች የሪፈራል አገልግሎት (MRS) የምክር አገልግሎት እንዲሁም የባህሪ ለውጥ ፕሮግራሞች፣ የወላጅነት ፕሮግራሞች፣ የአልኮል እና የሌሎች አደንዛዥ እፆች ፕሮግራሞች፣ የጤና ድጋፎች እና ማመቻቻ ድጋፍ አገልግሎቶችን የሚመለከት መረጃ ሊያቀርብልዎ ይችላል።
ይህን አገልግሎት በመላው ዓመት በሳምንት ለሰባት ቀናት እና በቀን ለ24 ሰዓታት ማግኘት ይቻላል፤ ስለዚህ በሚያስፈልግዎት ማንኛውም ሰዓት እርዳታ ማግኘት ይችላሉ።
የወንዶች የሪፈራል አገልግሎት ድጋፍ የሚያደርገው ለማን ነው?
- ከዚህ በፊት በደል የፈጸሙ ወይም በደል እየፈጸሙ የሚገኙ ወንዶች ባህሪያቸውን እንዲለውጡ።
- ወንዶች በፈጸሙት በደል የተጠቁ የቤተሰብ አባላት።
- ጥቃት እየፈጸሙ የሚገኙ ወይም የቤት ውስጥ እና የቤተሰብ ጥቃት ሰለባ የሆኑ ሰዎች ጓደኞች፣ ቤተሰብ ወይም የሥራ ባልደረባ የሆኑ እና እንዴት ድጋፍ ማድረግ እንደሚችሉ ማወቅ የሚፈልጉ ሰዎች።
- ጥቃት እየፈጸሙ ወይም እየደረሰባቸው የሚገኙ ደንበኞችን መደገፍ የሚፈልጉ ባለሙያዎች።
ወደ የወንዶች የሪፈራል አገልግሎት ሲደውሉ፦
- ማንነትዎ አይገለጽም
- አዳማጭ ያገኛሉ እንዲሁም አክብሮት በተሞላው መንገድ ይስተናገዳሉ
- ባህሪዎን በመለወጥ ረገድ ቀጣዮቹን እርምጃዎች ለመውሰድ ሊረዱ የሚችሉ በአካባቢዎ የሚገኙ አገልግሎቶች ዙሪያ መረጃ ያገኛሉ።
ድጋፍ ለማግኘት ወደ 1300 766 491 ይደውሉ። በተጨማሪም ከአገልግሎቱ ጋር ለመገናኘት እንዲረዳዎት በነፃ የሚቀርበውን የጽሑፍ ትርጉም እና የአስተርጓሚ አገልግሎት (Translating and Interpreting Service፣ TIS National) ወይም የእኛን ዌብቻት መጠቀም ይችላሉ።
አጭር የማማከር አገልግሎት (Brief Intervention Service)
አጭር የማማከር አገልግሎት (BIS) የወንዶች የባህሪ ለውጥ ፕሮግራም ለማግኘት እየተጠባበቁ ከሆነ ሊረዳዎት የሚችል ብሔራዊ የስልክ ጥሪ የምክር አገልግሎት ፕሮግራም ነው። ፕሮግራሙ በሚኖሩበት አካባቢ የማይገኝ ወይም እርስዎ እንግሊዘኛ መናገር የማይችሉ ከሆነም ሊረዳዎት ይችላል።
አጭር የማማከር አገልግሎት በበርካታ ክፍለ ጊዜዎች የሚከናወን ጊዜያዊ የስልክ ጥሪ ድጋፍ ፕሮግራም ነው። ፕሮግራሙ በሚከተሉት ነገሮች ረገድ ሊረዳዎት ይችላል፦
- ባህሪዎን ለመረዳት
- ለባህሪዎ ኃላፊነት መውሰድን እንዴት መማር እንደሚችሉ ለመዳሰስ
- ደኅንነታቸው የተጠበቀ እና ጤናማ የሆኑ ግንኙነቶች ማድረግ እና ደኅንነታቸው የተጠበቁ ቤተሰቦች መገንባት የሚቻልባቸው አዲስ ዘዴዎችን ለመማር።
አጭር የማማከር አገልግሎቶችን ማግኘት ከፈለጉ መጀመሪያ በ1300 766 491 ወደ የወንዶች ሪፈራል አገልግሎት መደወል ይኖርብዎታል። የምክር አገልግሎት ሰጪ ታሪክዎን አዳምጠው አጭር የማማከር አገልግሎት እንዲያገኙ ይረዱዎታል።
በተጨማሪም ከአገልግሎቱ ጋር ለመገናኘት እንዲረዳዎት በነፃ የሚቀርበውን የጽሑፍ ትርጉም እና የአስተርጓሚ አገልግሎት (Translating and Interpreting Service፣ TIS National) ወይም የእኛን ዌብቻት መጠቀም ይችላሉ።
የእርስዎ ግላዊነት እና ሚስጥራዊነት
የወንዶች የሪፈራል አገልግሎት እና አጭር የማማከር አገልግሎት የሚተዳደሩት በNo to Violence (NTV) ነው። No to Violence ጥራት ያለው አገልግሎት ለማቅረብ እና የእኛን አገልግሎት የሚጠቀሙትን ሁሉንም ሰዎች መብት ለማስከበር በቁርጠኝነት ይሠራል።
በ1988 የግላዊነት አዋጅ (Cth) መሰረት No to Violence የእርስዎን የግል መረጃ እንዴት ጥቅም ላይ እንደምናውል የሚገልጽ መረጃ ለእርስዎ ማቅረብ አለበት። የእርስዎ ወይም የሌሎች ደኅንነት ላይ ስጋት ካልተፈጠረ ወይም ይህንን መረጃ የማጋራት ሕጋዊ ግዴታ ከሌለብን በስተቀር መረጃዎ ግላዊ እና ሚስጥራዊ ተደርጎ ይጠበቃል።
እኛን በሚያነጋግሩበት ጊዜ እርስዎን ለመርዳት የግል መረጃዎ ጥቅም ላይ እንዲውል ፈቃደኛ መሆንዎን ይጠየቃሉ። አገልግሎቶቻችንን የሚያገኙ ሰዎችን የሚመለከቱ መረጃዎች ለምርምር ዓላማዎች እና ሪፖርት ለማዘጋጀት ጥቅም ላይ ሊውሉ ይችላሉ፤ ለምሳሌ ከእያንዳንዱ ስቴት ወይም ግዛት የሚደውሉት ሰዎች ብዛት። የስልክ ጥሪዎ የሚቀዳ ሲሆን፣ ለጥራት እና የሥልጠና ዓላማዎች ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል።
የእርስዎን መብቶች እና ግዴታዎች በተመለከተ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት እና የግላዊነት ፖሊሲያችንን ለማንበብ እባክዎ https://ntv.org.au/about-us/privacy/ን ይጎብኙ። እንዴት ግብረመልስ መስጠት ወይም ቅሬታ ማቅረብ ይቻላል የሚለውን የሚመለከት መረጃም ማግኘት ይችላሉ።
የጽሑፍ ትርጉም እና የአስተርጓሚ አገልግሎት (TIS National) ማግኘት የሚቻልበት መንገድ
የጽሑፍ ትርጉም እና የአስተርጓሚ አገልግሎት (TIS National) እንግሊዘኛ የማይችሉ ከሆነ እና የወንዶች ሪፈራል አገልግሎትን ማነጋገር ከፈለጉ ሊረዳዎ የሚችል ነፃ አገልግሎት ነው።
የTIS National አገልግሎትን ለመጠቀም፦
- በስልክዎ ወደ 131 450 ይደውሉ
- የሚያስፈልግዎትን ቋንቋ ለኦፕሬተሩ ያቅርቡ
- የሚያሻዎት ከሆነ የሚፈልጉትን የአስተርጓሚ ፆታ ይምረጡ (እንደ ተደራሽነታቸው የሚገኝ)።
ከወንዶች ሪፈራል አገልግሎት ጋር ለመገናኘት እንዲረዱዎ ኦፕሬተሩ ቋንቋዎን ከሚናገር አስተርጓሚ ጋር ያገናኙዎታል።
እባክዎ ውይይቱ ከ30 ደቂቃዎች በላይ ይወስዳል ብለው የሚያስቡ ከሆነ፣ ረዘም ያለ ቀጠሮ መያዝ እንዲችሉ ለአስተርጓሚው ያሳውቁ።
ዌብቻት
ኦንላይን ቅጽ በመጠቀም ከምክር አገልግሎት ሰጪ ጋር መነጋገርን የሚመርጡ ከሆነ የእኛን የወንዶች የሪፈራል አገልግሎት ዌብቻት መጠቀም ይችላሉ።
አገናኙ ላይ ጠቅ ካደረጉ በኋላ የዌብቻት ቅጹ ድረ-ገጹ ላይ በራስ-ሰር ይከፈታል። የእርስዎን ዝርዝር መረጃዎች ያስገቡ እና ከአገልግሎቱ ምላሽ እስኪያገኙ ድረስ ይጠብቁ።
እባክዎ የዌብቻት አገልግሎታችን የሚገኘው በእንግሊዘኛ ቋንቋ ብቻ መሆኑን ልብ ይበሉ። እንግሊዘኛ የማንበብ እና የመጻፍ ችሎታዎ ላይ የሚተማመኑ ከሆነ ይህ አማራጭ ለእርስዎ ተስማሚ ሊሆን ይችላል።
የተተረጎመው ድረ-ገጽ እና እዚህ የተዘረዘሩት አገልግሎቶች የገንዘብ ድጋፍ የሚያገኙት ከአውስትራሊያ የማኅበራዊ አገልግሎቶች የመንግሥት መምሪያ (Australian Government Department of Social Services) ነው።